Oduu Haaraya

ከኣቶ ያሬድ ጥበቡ ኦሮምያን ለሁለት የመግመስ ነፍጠኛዊ ‘ጥበብ’ በስተጀርባ

ስማቸው የተጠቀሰው ኣዛውንት ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ በወጣትነታቸው የተካፈሉ ናቸው። ሁዋላ ላይ ግን ከተሰለፉበት ሃይል ተለይተው ጉዋዶቻቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሲሆኑ እርሳቸው ስደት ላይ መሆናቸውን የግል ድረገጻቸው ላይ ይነግሩናል። ኣቶ ያሬድ ጥበቡን ለማስተዋወቅ ጊዜዪን የማባከን ግዴታ የለብኝም። ባጭሩ ግለሰቡ ቀደም ሲል ወያኔ ዛሬ ደግሞ ኣደገኛ ኒዮ-ነፍጠኛ መሆናቸውን በየመጣጥፎቻቸው ሁሉ የሚያንፀባርቁት ኣስተሳሰባቸው እየነገረን ነው። የሚገርመው ደግሞ ኣልፎ ኣልፎ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሲያገኙ እኔኮ እገሌ የሚባለው የኦሮሞ ዘር ነኝ እያሉ ማወናበድም ይታይባቸዋል። ለነገሩ በዛሬው ዘመን የምናያቸው የነፍጠኛው ስርእት ኣቀንቃኞች ወጣት ኣዛውንት ሳይለይ ኣንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ይሄው የተነቃበት ስልታቸው ነው። ኦሮሞን ለማታለል ሲከጅሉ ‘እኔምኮ በኣባቴ ወይም በእናቴ ኦሮሞ ነኝ’ ኣይነት ኣሰልቺ ፈሊጥ ተያይዘዋል።

ዛሬ ትኩረቴን የሳበው ኣቶ ያሬድ ጥበቡ ሰሞኑን ‘ምን ይሻላል?’ በሚል መጠይቃዊ ርእስ የፃፉት ጉዳይ ነው። በዚህ ፅሁፋቸው የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን በመሰሎቻቸው ዘንድ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የኖረን ውጥን ገሃድ ስላወጡት ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ ሆኖ ኣገኘሁት። እናም ይህ ፅሁፍ ያነጣጠረው በዋነኝነት ለኣቶ ያሬድ ጥበቡ ስብእና ክሬዲት ለመስጠት ሳይሆን እንደ እሳቸው ሁሉ ከኣንድ ኣይነት የትምክህት ፋብሪካ ተፈብርከው ኦሮሞነትና ኦሮምያን ለማጥፋት ደቦ ለሚጠራሩት ሁሉ ምላሽ እንዲሆን ነው።

እነ እቶ ያሬድን በጣም ኣስጨንቆኣቸውና ኣስጠብቦኣቸው ምን ይሻላል?’ ያስባላቸው ኦሮምያ በፍንፍኔ ላይ ያላት የባለቤትነት መብት ጉዳይ ነው። ወያኔ ካልተገበርኩት ብሎ የፎከረውን የፍንፍኔ ማስተር ፕላን በተመለከተ ነው የነኣቶ ያሬድ ጭንቀት። ታዲያ ግለሰቡ ‘ምን ይሻላል?’ ብለው ፅሁፋቸውን መጀመራቸውን ብቻ ያየ የዋህ ሰው ምናልባት እኒህ ሽማግሌ የኦሮሞ ህዝብ በማስተር ፕላኑ ሳቢያ ከቀዬው ላይ የመፈናቀሉ ጉዳይ ኣሳስቦኣቸው የኣረጋዊነት ኣስታራቂ ኣስተዋፅኦ ለማበርከት ኣስበው ይሆን ብሎ መጠየቁ ኣይቀርም። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። የነፍጠኛውን ተጠባቢ ያሬድ ጥበቡን ያስጠበባቸው እንዴት ኦሮሞ በሸገር ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳል የሚለው እንጂ የኦሮሞ በገዛ ኣገሩ ላይ መበደልና መገፋት ኣይደለም።  ታዲያ ኣሃዱ ብለው ፅሁፋቸውን የጀመሩትም እንዲህ በማለት ነበር።

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በብዙ ጉዳዮች የሚለያዩ ቢሆንም፣ ፊንፊኔ መናገሻችን ናት በሚለው ጉዳይ ግን ይስማማሉ ለዚህም ይመስላል በአዲስ አበባ ማስተርፕላን ጉዳይ፣ ኦሮሞ ፈርስትና ኦፒዲኦ እጅና ጓንት ሆነው ሃገሩን ያተራመሱት ለመሆኑ ፊንፊኔ የኦሮሞ መናገሻ ነበረች? ኦሮሞዎች ከየት መጡ?” 

በዚህ ኣባባላቸው ሁለት ድንጋዮችን ኣንስተው ኦሮሞ ላይ ወርዉረዋል ግለሰቡ። ኣንደኛው የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነቶች እያሏቸው ነገር ግን ኣንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ መገኘቱ ኣቶ ያሬድን በጽኑ እንዳበገናቸው ከዚህ ኣባባላቸው እንረዳለን። ሌላው ደግሞ ግለሰቡን ክፉኛ የወገራቸው የነፍጠኝነት ጠኔ ኦሮሞ ኣገሩእዚህ ኣይደለም የሚለው የበሰበሰና የበከተ የኣባቶቻቸው ተረት ተረት ነው። ለዚህም ነው ለመሆኑ ፊንፊኔ የኦሮሞ መናገሻ ነበረች? ኦሮሞዎችስ ከየት መጡ?’ እያሉ ቆርፋዳ ጥያቄ የሚያነሱት።

ኣቶ ያሬድ የኣባቶቻቸውን ስልት በመከተል ኦሮሞን በኦሮሞ ለመምታትም ሞክረዋል። መርዛቸውን ለመትፋት ዋቢ መጥራት የፈለጉት የፊውዳል ነፍጠኛው እሽከር ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩት የይልማ ዸሬሳን ቅዠታዊ ድርሰት ነው። ስለ ኣቶ ይልማ ዸሬሳ ማንነት ለጊዜው ኣሁን ማንሳት ኣልፈልግም። ኣቶ ያሬድ ይቀጥላሉ። ዋነኛ መከራከሪያቸውም ኦሮሞ ኣገሩ ኣሁን ካለበት መሬት ላይ ኣይደለምና የፍንፍኔን የባለቤትነት መብት እርግፍ ኣድርጎ መተው ኣለበት ነው። እኛ እዚህ ኣካባቢ ላይ የ3000 ኣመት ታሪክ ሲኖረን እናንተ ኦሮሞዎች ግን 500 ኣመት ኣልደፈናችሁም ሊሉን ዳድተዋል። እዚህ ጋር ሳቄ መጣ። የ3000 ኣመቱን የጥንታዊት ኩሽ-ላንድን (ኦሮሞና ኑቢያን ያካተተ) ስልጣኔ ሴማዊያኑ ሃበሾች ትላንት ከደቡብ ኣረቢያ ፈልሰው መጥተው በመንጠቅ የታሪኩ ባለቤት የሆነውን የኩሽ ታላቁ ግንድ ኦሮሞን ኣገርህ እዚህ ኣይደለም ሲሉት መሳቅ ነው ኣንጂ የምን መገረም! በመጽሃፍ ቅዱስ ሁሉ ሳይቀር በእብራይስጥ ቁዋንቁዋ ‘Cush shall soon stretch her hands unto God’ የተባለውን ይሉኝታ ቢሶቹ ሃበሾች ጠምዝዘውት ባለታሪኮቹን ኩሾች ወደ ጎን በመተው ራሳቸውን የስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጣቸውና ‘እኛኮ ስማችን መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይቀር የተጠቀሰ ክቡር ዘሮች’ ነን ሲሉ ነው የሚያስቀኝ። ታላቁ ኣባታችን የሚሉት ዳግማዊ ምኒልክ እኔ ኣፍሪቃዊ ወይም ከጥቁር ነገድኣይደለሁም በማለት እሱና ዘርማንዘሩ ለከተሙበት ሸገርም ሆነ ኣገር እንግዳ መሆናቸውን በራሱ ኣንደበት ሲመሰክር ኣልሰሙም ወይም ኣላነበቡም ይሆናል ጠቢብ ነኝ ባዩ የኣቶ ጥበቡ ልጅ።

እናም ቀጠሉ። ይህ ሁሉ ድካማቸው ደግሞ ወደሚቀጥለው ፍሬ ጉዳይ ለመግባት ነው። ፍንፍኔን ከኦሮሞ ለማስጣልና ከፍንፍኔም ኣልፎ ሰፊውን የከተማዋ ዙሪያ የኦሮምያ ለም መሬት ለመንጠቅ ‘ብዙ ተጠበብኩለት’ ያሉትን ‘ጥበብ’ መተንተን ይጀምራሉ። ከዚያ በፊት ግን ልክ ኣንደ ትላንቱ ኣባቶቻቸው ሁሉ ለኦሮሞ ህዝብና ይህ ህዝብ በትግሉ ስለከፈላቸው መስዋእትነቶች ያላቸውን ንቀት ልብ እንበል።

ፊንፊኔ ከከብት አርቢዎች ሆራነት ወጥታ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መናገሻ የሆነችው በመላ ኢትዮጵያውያን ትጋትና ድካም መሆኑ እየታወቀ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያክልል ውስጥ ናት የሚል ወያኔአዊ ደባ ምን ይጠቅማል?”

የመሸባቸው ነፍጠኛ በዚህ ኣባባላቸው ኣሁንም ሁለት ድንጋይ ወረወሩ። ኣንደኛው ፊንፊኔን ኣስታክከው ኦሮሞን ‘ከከብት ኣርቢነት ያልዘለለ ስልጣኔ ያልነበረው ህዝብ’ የሚል ኣይነት ዘለፋ ያዘለ መልእክት ለመላክ ያለመ ኣባባል ነው። ሁለተኛው ንቀታቸው ደግሞ ፊንፊኔ ኦሮምያ ክልል ውስጥ ናት መባሉ ‘የወያኔ ደባ’ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ተፈጥሮኣዊ ኣሰፋፈርና በህዝቡ ትግል የተረጋገጠ ስያሜ መሆኑን ልባቸው እያወቀው መካድ መረጡ።

በዚህ መንደርደሪያ ነው እንግዲህ ቀቢጸ-ተስፋነታቸውንና የኦሮሞ ህዝብ ደመኛ ጠላትነታቸውን ፍንትው ኣድርጎ ወደሚያሳየው ‘መፍትሄ’ኣቸው የተሻገሩት። ‘ኣንዱ የሚታየኝ መፍትሄ’ በማለት ይጀምራሉ።

አንዱ የሚታየኝ መፍትሄ አሁን ባለው ፌዴራላዊ አወቃቀር ውስጥ የአዲስ አበባ ነዋሪ ዜግነቱን የሚያገኝበት መንገድ ማፈላለግ ነው ለዚህም፣ ማዘጋጃ ቤቱን እንደማእከል ወይም መነሻ በመውሰድ፣ 150 ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ያለውን ግዛትየማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልልብሎ 10 ክልል መጨመርና፣ ይህም ክልል በፌዴራልምክርቤት ድምፅ እንዲኖረው ማድረግ

ይህ እንግዲህ የኣላማቸው ኣከርካሪ መሆኑ ነው። እነ ኣቶ ያሬድ በዚህ ‘መፍትሄ’ ባሉት ሃሳብ ያተኮሩት በኣንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በዋነኛነት ሁለት ጥቅሞችን ለማካበት መሆኑ ያሳብቅባቸዋል። ኣንደኛው ወያኔንና የነፍጠኛውን ስርኣት ናፋቂዎች የሚያስታርቅ ‘ድንቅ ሃሳብ’ ማፍለቅና ሁለቱ ሃይሎች ተደጋግፈው ኦሮሞና ሌሎችም ነጻነት ናፋቂ ህዝቦች ላይ እንዲያነጣጥሩ የምክር ኣገልግሎት መስጠት ነው። ወያኔ የገዛ ህገ-መንግስቱን ረግጦ ፍንፍኔን ከኦሮሞ ህዝብ ለመንጠቅ ያሳየውን ፍላጎት ከቀድሞው ስርእት ናፋቂዎች ኣላማ ጋር መሳ ለመሳ በማስኬድ ወይም ኣንድ ላይ በማቀናጀት ኦሮሞን ነጥሎ መምታት። ኣሁን ያለው የወያኔ ፌዴራላዊ ኣወቃቀር እንደተጠበቀ ሆኖ የቀድሞው ስርእት ናፋቂዎች በፍንፍኔ ላይ ያላቸው ኢ-ፍትሃዊ የባለ ርስትነት ጥያቄ የሚመለስበትና በዚህም እርምጃ ኦሮሞንና የኦሮሞነትን ህልውና ከዋና ከተማይቱ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ማባረርን ያካተተ ‘መፍትሄ’ መሆኑ ነው። እነ ኣቶ ያሬድ ይህን ሲያስቡ ከወያኔ ጋር እርቅ ፈጥረው ከስደት ኣለም ወደናፈቀቻቸው ኣገራቸው ሞት ሳይቀድማቸው ለመመለስ የተጣደፉ ይመስላሉ። ከኦሮሞ ተፅእኖ ነጻ በሆነች ‘እዲስ እበባ’ ላይ የሃረር ሰንጋ ጮማ እየቆረጡና በጉደር ወይን ጠጅ እያወራርዱ በምንጃር እስክስታ ኣቧራ ሲያነሱ በኣእምሮኣቸው ውልብ እያለባቸው መሆኑን መገመትም ይቻላል።

ኒዮ-ነፍጠኛው ‘መፍትሄ’ ብለው ባነሱት በዚህ ሃሳብ ሌላው በዋነኝነት ያነጣጠሩት በ‘150 ኪሎ ሜትሩ ሬዲዬስ ግዛት’ ጉዳይ ላይ ነው። የ150 ኪሎ ሜትሩ ሬዲዬስ ሃሳብ ሁለት ግዙፍ ኣላማዎችን ተሸክሟል። የመጀመሪያው ከላይ እንደተጠቀሰው በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ ኦሮሞንና የኦሮሞነትን ህልውና ማስወገድ ሲሆን ሁለተኛውና እጅግ ዋነኛው ምኞት ኦሮምያን ለሁለት የመግመስ የቆየ ህልም ነው። የኣቶ ያሬድ ቅዠት ከተሳካና የ‘150 ኪሎ ሜትር ሬዲዬሱ 10ኛ ክልል’ ከተዋቀረ ታላቁዋ ኦሮምያ ታላቅነቷና ኣንድነቷ ኣክትሞ ምእራብና ምስራቅ ላይ ለሁለት ትገመሳለች።

የጠላቶቻችን ትልቁ ኣላማ እዚህ ላይ ነው። ለሁለት የተገመሰች ኦሮምያን ከማየት የበለጠ ከሰማይ በታች በደስታ የሚያሰክራቸው ክስተት ያለ ኣይመስልም። ለዚህም ነው በፊንፍኔ ጉዳይ ላይ ከኦፒዲኦ ኣስከ ኦነግ ባሉት የኦሮሞ ድርጅቶች መሃል ኣንድ ወጥ እምነት መኖሩ እንደ እሳት የሚያንገበግባቸው።

እንደዚህ ኣይነቱ መርዘኛ ኣመለካከት የሚመጣው ኣንድም ከትምክህተኝነት ውርስ ኣልያም የኦሮሞ ህዝብ የብሄረተኝነት ስሜትና ቁርጠኝነት ዛሬ ሊቀለበስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ካለመረዳት ወይም በሁለቱም ምንክያቶች ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ግን ከንቱ ቅዠት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ኣንድነትና የኦሮምያ ካርታ በያንዳንዱ የኦሮሞ ተወላጅ ልብ ውስጥ ታትሞኣል። ዛሬ ከኦነግ እስከ ኦፒዲኦ ድረስ ያለው እያንዳንዱ የኦሮሞ ዜጋ በኦሮምያ ሉኣላዊነት ላይ ከማንም ጋር ኣይደራደርም። ኣቶ ያሬድና መሰሎቻቸው ቅዠታቸውን ኣቁመው ይህንን ሃቅ እየመረራቸውም ቢሆን መዋጥ ይጠበቅባቸዋል።

እነዚህ ወገኖች ዛሬም በለመዱት የብልጣብልጥነት መንገድ መሄዱ የሚያዛልቃቸው መስሎኣቸዋል። የኦሮሞነትን የኣገር ባለቤትነት ህልውና ከ150 ኪሎ ሜትር ሬዲዬስ ውስጥ ገፍተው በማስወጣት ሸገር ላይ መንገስና መፈንጠዝ ከቼዝ ጨዋታ የቀለለ ተግባር መስሎ ታይቶኣቸው ይሆናል። የኦሮሞ ልጆች ዛሬም ድረስ የኣገራቸውን የፊንፊኔንና የኣካባቢውን ሉኣላዊነት በውድ ደማቸው እያስከበሩና ወደፊትም እንደሚያስከብሩ ኣኒህ ሸበቶና መሰሎቻቸው ከእድሜ ዘመናቸው ገና ኣልተማሩም። ሌላው ቀርቶ ኣምና በሚያዝያ ወር እሳቸው ‘ከኦሮሞነቱ ይልቅ ኢትዮጵያዊነቱን ያስቀድማል’ ያሉት የማእከላዊ ኦሮምያ ህዝብ በኣምቦና በሌሎችም የኣካባቢው ከተሞች የወያኔን ማስተር ፕላን በመቃወም ወደር የሌለው ጀግንነቱን ኣሳይቷል። ይህ ኣንድ ኣመት ኣንኩዋን ባልሞላውና ከመቶ የማያንሱ የቁርጥ ቀን ልጆቻችን የህይወት ዋጋ የከፈሉበት ገድል የሚያስተላልፈው መልእክት ለነ ጥበቡ ልጅም ሆነ ለመሰሎቻቸው ኣይገባቸውም። እንዲገባቸውም ኣይፈልጉም። ወደፊትም በቀሪው የህይወት ዘመናቸው ኦሮሞንና ኦሮምያን በውል ለማወቅ ኣይኖቻቸውንና ጆሮዎቻቸውን ለመክፈት የተዘጋጁ ኣይመስሉም።

ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ሸበቶዎቹ ትምክህተኞች ይህን የጠነባ ኣመለካከታቸውን እንደወረደ ለመከረኞቹ ልጆቻቸው እያወረሱት መሆኑ ነው። ኦሮምያን ለሁለት ለመግመስና ብሎም ከካርታ ላይ ለማጥፋት በያዙት ከንቱ ቅዠት ተጠምደው የራሳቸውን ቤት ማበጃጀት ተስኖኣቸዋል። ከኣቶ ያሬድ ጥበቡ ‘150 ኪሎ ሜትር ራዲዬስ’ ፎርሙላ በስተጀርባ የተሰለፉት የነፍጠኛ ልጆች ሁሉ እጃቸውን ከኦሮምያ ላይ ኣንስተው እዛው ክልላቸው ውስጥ ሰላምና እኩልነትን ላማስፈን በቅንነት ቢዘጋጁ ያዋጣቸዋል። የነርሱ ትምክህት ፈልሰው በመጡት በኦሮምያ ምድር ብቻ ሳይሆን ያያት ቅደመ ኣያታችን ርስት ኣያሉ በሚመጻደቁበት ቀዬኣቸው ሳይቀር ለዘመናት ኣፍነው ያቆዩዋቸውን ጥንታዊያን ብሄር ብሄረሰቦችን ለመብታቸው መከበር እያነሳሳቸው ይገኛል። ጎንደር ውስጥ የቅማንት ህዝብ ይህን በሚመስል ኣስገራሚ ቁርጠኝነት ተደራጅቶ ይታገላል፣ መብቱንም ይጎናጸፋል ብሎ የጠበቀ ኣልነበረም። ግን ይሄው ታሪክ ኣይናችን ስር ሲሰራ ኣየን። ኣገውም ቢሆን ኣሁን በታጠረለት ልፍስፍስ ኣጥር ተገድቦ ዘላለም የሚቀጥል ህዝብ ኣይደለም። የትላንቱን የ10ኛው ክፍለ ዘመን ጀግንነቱን መድገሙ የጊዜ ጉዳይ ነው። የጀግኖች ምድር የሆነው ወሎም እንዲሁ የዘመነ መሳፍንቱን ኣይነት ጀግንነት መድገም ባያስፈልገውም ባለበት በወሎ ምድር የራሱን ብሄራዊ ማንነትና ቁዋንቁዋ ለማስመለስ ‘ኣሃሃሃኮርማንጋፎ ብሎ የሚነሳበት ጊዜ ሩቅ ኣይሆንም። ሌላውም ኣንዲሁ።

Check Also

faannoo

OROMO CIVILIANS CONTINUE TO BE TARGETED BY FANO MILITIA

Amhara Fano continued to attack Oromo civilians. In this latest incident, at least 17 people …